Sunday, 13 April 2014

የቀለም አብዮት

የቀለም አብዮት
ኢቲቪ የሰራውን “የቀለም አብዮት” ዘጋቢ ፊልም በወፍ በረር አይቼዋለሁ። አዲስ አይደለም። ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በአይጋ ፎረም ላይ ሲወጡ የነበሩ ጽፎች በምስል ተቀነባብረው ነው የቀረቡት።
የፊልሙ ቀዳሚ አላማ ፍርሃትን በመልቀቅ ህዝቡ ለመብቱ እንዳይታገል ማኮላሸት ነው ። ፈረንጆቹ fear mongering ( scaremongering) የሚሉት ነው። “መንግስትን እንገለብጣለን ብላችሁ ብታምጹ የዩክሬን እጣ ይደርሳችሁዋል” የሚል ፍርሃት ነው ሲለቀቅ ያየነው ። እንዲያውም በቅርቡ አንዱ የህወሃት/ኢህአዴግ ጸሃፊ “አመጽ ከተነሳ ክልሎች ይገነጠላሉ፣ ስልጣን የሚይዘው ሃይልም ከአዲስ አበባ ውጭ ስልጣን አይኖረውም፣ ” በማለት የጻፈውን አንብቤአለሁ። መለስ በ1997 ዓም በጻፈው አንድ ጽሁፍ ላይ ተመሳሳይ ነገር ተናግሮ ነበር፤ ጁኔዲን ሳዶም “ ነፍጠኛው ተመልሶ ስልጣን የሚይዝ ከሆነ ኦሮምያን እንገነጥላለን” ብሎ ነበር። ነፍጠኛ የተባለው ቅንጅት ነው። አምባገነኖች ሁሌም “እኛ ከሌለን ጸሃይ ትጠልቃለች” ይላሉ። አንድም ቀን ግን አምባገነኖች ወድቀው ጸሃይ ስትጠልቅ አላየንም። በኢትዮጵያም አትጠልቅም። ኢህአዴግ ቢወድቅ ኢትዮጵያ አትበታተንም! ምክንያቶቼን በሌላ ጊዜ አቀርባለሁ።
ፊልሙ ሌሎች መለስተኛ ግቦችን ለማግኘት ተብሎም የተዘጋጀ ነው። አንደኛው አሜሪካን “ማስጠንቀቅ” ነው፤ “ አሜሪካ አመጽ ለማስነሳት ስታሴሪ ደርሰንብሻል” ሊሏት ይፈልጋሉ።አይጋ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ “የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መንግስታዊ ካለሆኑ የውጭ ድርጅቶች ጀርባ ሆኖ አመጽ ለማስነሳት እየሰራ ነው” ሲል ገልጾ ነበር። የሰማያዊ ፓርቲ መሪ የአፍሪካ ወጣት መሪ ተብሎ መመረጡ፣ የስቴት ዲፓርትመንት ጠንካራ ሪፖርት፣ በቅርቡ በኮንግረስ የጸደቀው ህግ ፣ አሜሪካ ኢሳትን ለማስቆም ፍላጎት አለማሳየቷና መንግስትን በሃይል ለመጣል የሚታገሉ ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶች አቅፋ መያዙዋ ኢህአዴግን አናዶታል። ባለኝ መረጃ አሜሪካ እና ኢህአዴግ፣ ይፋ ባያወጡትም ሆድና ጀርባ ሆነዋል። ህወሃቶች አሜሪካ ከጀርባችን ሆና በስለት እየወጋችን ነው ብለው ያምናሉ። የህወሃት አሜሪካን ማስጠንቀቅ ተንጋሎ እንደመትፋት ነው። አስቂኙ ነገር ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን የአሜሪካ ተላላኪ አድርጎ ለመፈረጅ የተደረገው ሙከራ ነው። ኢህአዴግ በተቃዋዎች አይን ውስጥ ያለውን ብናኝ አቧራ ለማየት ከሚሞክር በራሱ አይን ውስጥ ያለውን ግንድ ቢመለከት ይበጀዋል።
ፊልሙ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችንም ለማስደንገጥ ተብሎ የተሰራ ነው። በተለይ ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች ጥርስ ውስጥ ገብተዋል። እንዲያውም ዛሬ የወጣ የህወሃት ጽሁፍ “ ግንቦት 7 እና ኢሳት ከሰማያዊ ፓርቲ ጀርባ አሉበት” ብሎአል። በባህርዳር፣ ደሴ፣ አዲስ አበባ የተካሄዱት ሰልፎች አልጋውን ማረጋጋት የተሳነውን ህወሃት አስደንግጠውታል። በጥቂት የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎችና የነጻው ፕሬስ አባላት ላይ የተለመደው የአፈና እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ኢህአዴግ የትግል መሪዎችን በማሰር ትግል የሚቆም ይመስለዋል። የሰማያዊና አንድነት መሪዎች ተተኪዎቻቸውን በሚስጢር ሳያዘጋጁ እንዲህ አይነት ትግል ውስጥ አይገቡም። በስራ ጫና ወይም በቼልታ የተነሳ ተተኪዎቻቸውን መርጠው ካልሆነም ጊዜው አሁን ነው። ከቅንጅት ድክመት መማር ነው።
ፊልሙ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ ተብሎ መዘጋጀቱንም እናያለን። የኢትዮጵያ ህዝብ በኑሮውና በፍትህ መጓደል እጅግ ተማሮ ይገኛል። የ5 አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በወረቀት ላይ መቅረቱ ታይቷል፤ ለታይታ የተሰሩት ግንባታዎችም የህዝቡን መሰረታዊ ችግር የሚቀይሩ አልሆኑም። ህዝቡ በህወሃት አመራር አዲስ ነገር ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረጉን አቁሟል። ከገጠር እስከ ከተማ የለውጥ ድምጽ ያስተጋባል። ኢህአዴግም በህዝቡ የዝምታ-ጩኸት ስጋት ውስጥ ወድቋል። ያንን ስጋቱን ዛሬ አደባባይ አውጥቶታል። “ኢህአዴግ ከሌለ ሰላምና ደህንነት አይኖርም፣ ስለዚህ ህዝቡ ኑሮ እያማረረውም ቢሆን ለሰላሙ ሲል ኢህአዴግን ታቅፎ ይቀመጥ” ሲል የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ተፍጨርጭሯል።
ይህ ዘጋቢ ፊልም ህዝቡን የማስፈራራት ሃይሉ እጅግ አነስተኛ ነው። እንዲያውም በተቀራኒው ለለውጥ እንዲነሳ ያበረታታዋል ብየ አስባለሁ። ህዝቡ ኢህአዴግ በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ መሆኑን አይቷል። ይህ ደግሞ የወጣቱን ልብ ይበልጥ እንዲነሳሳ ያደርገዋል።
ፊልሙ የኢህአዴግን ካድሬዎችም የሚያስደነግጥ ነው። ድርጅታቸው በዚህ መጠን ከፈራ ከእንግዲህ ምን ተስፋ አላቸው? ካድሬ ያገኘውን እየዘረፈ መሸሹ አይቀሬ ነው፣ ጭሱን እንዳለ አረጋግጧልና።
ህወሃት በቀሩ እድሜው እንደ አበደ ውሻ ሁሉንም ለመላከፍ መሞከሩ አይቀርም፡፤መድሃኒቱ በአንድነት መነሳት ነው። አንዱ መስዋት ሲሆን ሌላውን እየተካ፣ መሪና ተመሪ እየሆኑ እስከ ድል መጓዝ ነው። አሁን የሚታየው ትግል ተጠናክሮ ከቀጠለ፣ ነጻይቱ አገር፣ ያለ ብዙ ምጥ፣ በቶሎ ትወለዳለች ።

No comments:

Post a Comment