Friday, 29 August 2014

አርከበ እቁባይ፣ በረከት ስምኦን፣ አባ ዱላ ገመዳ፣ ሳሞራ የኑስ፣ አባይ ጸሃየ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ፣ ሃሰን ሺፋ፣ ሙሉጌታ በርሄ፣ ነጋ በርሄ፣ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ኮማንደር ሰመረ እና አንድ ስሙ ያልተገለጸ ሰው በምርጫ 97 ማግስት ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ፣ እንዲደፈሩ፣ እንዲታሰሩ፣ ከስራቸው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ እንዲሁም አንዳንዶች ታፍነው እንዲወሰዱ ትእዛዝ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተከሰሱበት የክስ መዝገብ ለስዊድን አለማቀፍ ወንጀል መርማሪ ፖሊስ ተሰጠ

ነሃሴ ፳፪(ሃያሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምርጫ 97 ለተገደሉት እና ለቆሰሉት ፍትህ ለመጠየቅ የተቋቋመው ግብረሃይል ስራውን አጠናቆ ዛሬ የ13
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትንና የመከላከያ ሰራዊት አዛዦችን ስም ዝርዝር የያዘ የክስ ማመልከቻ ለስዊድን አለማቀፍ የጦር ወንጀል መርማሪ ፖሊስ አስረክቧል።
አርከበ እቁባይ፣ በረከት ስምኦን፣ አባ ዱላ ገመዳ፣ ሳሞራ የኑስ፣ አባይ ጸሃየ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ፣ ሃሰን ሺፋ፣ ሙሉጌታ በርሄ፣ ነጋ በርሄ፣ ወርቅነህ
ገበየሁ፣ ኮማንደር ሰመረ እና አንድ ስሙ ያልተገለጸ ሰው በምርጫ 97 ማግስት ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ፣  እንዲደፈሩ፣ እንዲታሰሩ፣ ከስራቸው እንዲፈናቀሉና
እንዲሰደዱ እንዲሁም አንዳንዶች ታፍነው እንዲወሰዱ ትእዛዝ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የክስ ቻርጁ ለፖሊስ መቅረቡን ተከትሎ ቃለ መጠይቅ ያደረግንላቸው ጉዳዩን በማስተባበርና በመምራት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት አቶ ሞላ ይግዛው እንደገለጹት፣
የስዊድን አለማቀፍ ወንጀል መርማሪ ፖሊስ በቀረበው የክስ ጭብጥና በቀረቡት የሰነድና የቪዲዮ ማስረጃዎች መርካቱን ገልጿል። ምርመራውን የያዙት ከዚህ ቀደም
በዩጎዝላቪያ፣ ሩዋንዳና በሌሎችም አገራት የተፈጸሙትን ወንጀሎች የመረመሩና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፖሊስ  ሲሆኑ፣ እርሳቸውም ለግብረሃይሉ ምርመራውን
ዛሬውኑ መጀመራቸውን ማስታወቃቸውን አቶ ሞላ ገልጸዋል።
ስዊድን የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ለመክሰስ ምን ስልጣን አላት? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሞላ  ፣  “የስዊድን ፓርላማ በየትኛውም አገር የተፈጸመ የጦር ወንጀል
እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በስዊድን ፍርድ ቤት እንደሚታይ በቅርቡ መወሰኑ ክሱን ለመመስረት ምክንያት መሆኑን ” ገልጸዋል።
የስዊድን ፖሊስ ምርመራውን እንዳጠናቀቀ ለአቃቢ ህግ እንደሚያስተላልፍና አቃቢህግም በስዊድን አለማቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሰረት አቶ ሞላ ገልጸዋል።
ፖሊስ የሚያካሂደው የምርመራ ውጤት፣ እስካሁን ከተሰባሰቡትና ለወደፊተም ከሚጨመሩት ሰነዶች ጋር ተያይዞ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት
እንደሚቀርብና ምክር ቤቱም በአለማፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲታይ ትእዛዝ እንዲሰጥ ጥያቄ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።
የአሁኑ ክስ በግለሰብ ባለስልጣናት ላይ የቀረበ ቢሆንም፣ ሌሎች ክሶች በተከታታይ እንደሚቀርቡና ክሱ የኢትዮጵያን መንግስት እንደሚያካትት የገለጹት አቶ ሞላ፣ መንግስት
በሚከሰስበት ጊዜ በውጭ አገር የሚያንቀሳቅሰው ሃብቱ እንዲታገድ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
አሁን የቀረቡት ተከሳሶች 13 ብቻ ቢሆኑም በሂደት እንደሚጨምሩ የገለጹት አቶ ሞላ፣ በወቅቱ በአዲስ አበባ እልቂት ለመፈጸም የመጡት የ34 ባታሊዮን ጦር አዛዦች
ስም እንደሚፈለግና የእነዚህን አዛዦች ስም የሚያዉቁ እንዲናገሩ ጠይቀዋል።
በኦጋዴን ለተፈጸመው ገድያ እጃቸው አለበት የተባሉ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማደን በኢንተርፖል በኩል እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ሞላ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ከ13 ተከሳሾች መካከል የአንደኛው ስም ሆን ተብሎ እንዳይገለጽ መደረጉን አቶ ሞላ ተናግረዋል።
የክሱ መመስረት ፍትህ አጥቶ ለቆየው ኢትዮጵያዊ መልካም ዜና መሆኑም አቶ ሞላ ገልጸዋል።
ከአቶ ሞላ ጋር የተደረገው ሙሉ ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ ይቀርባል።
ዜናው በኢሳት ሰበር ዜና ከቀረበ በሁዋላ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ አስተያየቶችን ስልኮችን በመደወል እየሰጡ ነው።

No comments:

Post a Comment