በቀለ ጅራታ:- በኢትዮዽያ የትምህርት ቤት ህጻናት በመንግስት ሃይሎች ደማቸው ሲፈስ እየታዬ ዝምታን የሚመርጥ ኣንጀት ሊኖር ኣይገባም።
Posted: Muddee/December 4, 2015 · Finfinne Tribune | Gadaa.com | Comments (3)
በበቀለ ጅራታ* | (የኦፌዴን የቀድሞ ዋና ፀሐፊ)
ይህ የኣሁኑ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ሟቋረጥ የበርካታ ዜጎችን ህይዎት ኣጠፍቷል። በተለይም በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የተፈጽሙት ግዲያዎች፣ የጅምላ እስርና ማሰቃየት ተነግሮና ተጽፎ የሚያልቅ ኣይደለም። ይህ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ በተለዬ ሁኔታ ሆን ቢሎ ነገር እየፈለገ በሰላም እንዳይኖር በማድረግ በገዛ ሃገሩ ግፍ እየፈጸመበት ይገኛል። የዛሬ ኣስራ ኣምስት ኣመት ኣካባቢ ሆን ቢሎ የክልሉን መንግስት ዋና ከተማ ከኣዲስ ኣበባ ወደ ኣዳማ እንዲቀየር በማለት በማናለብኝነት የወሰነውን ውሳኔ በሰላማዊ መንገድ በመቃወማቸው በርካታ የክልሉ ተማሪዎችን በግፍ ጨፈጨፈ።
በሺዎች የሚቆጠሩትን በተለያዩ እስር ቤቶች በማጎር በድብደባና በህክምና እጦት በርካቶች በእስር ቤቶች ውስጥ እንዲሞቱ ተደረገ። ከዚያም ጊዜ ወዲህም ምክንያት እየተፈለገ በርካቶች በእስር ቤቶች እየታጎሩ የበደሎች በደል ሲፈጸምባቸው ኖረዋል።
ከቅርብ ኣመታት ወዲህ ደግሞ በልማት ስም የገበሬውን መሬት ለውጪ ባለሃብቶች በመሸጥ ከኖሩበት በማፈናቀል ለከፋ ችግርና መከራ ሲዳርግ ቆይቷል። ይህንን ህገወጥ ድርጊት የተቃወሙትንም በእስር ሲያንገላታ ኖሯል። ካለፉት ሁለት ኣመታት ወዲህ ደግሞ ኣዲስ ኣበባን ለማስፋት የሚል ኣዲስ ምክንያት በመፍጠር በኣዲስ ኣበባ ከተማ ዙሪያ ያሉትን የገበሬውን መሬቶች ወደ ከተማው ለመቀላቀል የወጠነውን የማስተር ፕላን እቅድ በሰላማዊ መንገድ የተቃወሙትን ህጻናት ሳይቀሩ ያለሟቋረጥ በጭካኔ በመፍጀት ላይ ይገኛል። የኦሮሞ ተማሪዎችም ሆኑ መላው የኦሮሞ ህዝብ የሚቃወሙት በማስተር ፕላን ሰበብ ነባሩ ነዋሪ ህዝብ መፈናቀል ኣይገባውም፣ የሃገር ልማት ህዝቡን ለዘመናት ከኖረበት ቄዬ በማፈናቀል ሳይሆን መከናውንያለበት ህዝቡን ጭምር የሚያለማና ኑሮውን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆን ኣለበት በሚል ነው እንጂ ልማትን በመቃወም ኣይደለም።
ኣዲስ ኣበባ መሃሉ ገና ምንም ባልለማበት ሁኔታ ላይ እያለ ከዚያ ውጭ ብዙ ኪሎሜትሮች በመሄድ የኣርሶ ኣደሩን ህይዎት ለማናጋትና ከገዛ መሬቱ ለማፈናቀል የተፈገበት ምክንያት እንደተለመደው ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥና ለመክበር ካልሆነ ሌላ እንዳልሆነ ማንም ያውቃል። በዚህ ማስተር ፕላን ሰበብ የኦሮሞ ህጻናትን በመፍጀት “ታላቁ መሪያቸው” ያስቀመጠውን “ብዙሃንን ኣናሳ ማደረግ ይቻላል” የሚለውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ መንግሥት ባለፈው ኣመት በኣምቦ፣ በኣዳማ፣ በባሌ ሮቤ ወዘተ የበርካታ የኦሮሞ ተማሪዎችን ያለ ርህራሄ ፈጃቸው። ይሄው ዘንድሮም ካለፉት ጊዜያት በከፋ መልኩ የኣንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን በእናቶቻቸዉ ፊት ሳይቀር በሳንጃ እየቀደዳቸው ሬሳቸውን በየሜዳው በትኖ በማሳየት ላይ ነው። እንደዚህ ኣይነት ድርጊት የሃገሪቷ መንግስት ነኝ ከሚል ኣካል ቀርቶ ከውጭ በመጣ ጠላትም ኣይፈጸምም። እድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ይህንን የግፍ ኣገዳደል ለመደበቅ ቢሞክርም ፈጽሞ ኣይችልም። ሁሉ ነገሩ ገዳዮቹ በቦታው ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሄዱ ለኢትዮዽያ ህዝቦችና ለኣለም ህብረተሰብ እየደረሰ ይገኛል።
ይህ መንግስት ከላይ እንዳልኩት ባለፉት ሃያ ኣምስት ኣመታት ያለሟቋረጥ በማን ኣለብኝነት ሃገሪቷን ሰላም እየነሳ እዚህ ደርሷል። ሆኖም የሃገሪቷ ህዝቦች ተባብረው በቃህ ልሉ ኣልቻሉም። ምንም የማያውቁ ህጽናት በግፍ መንግስት ባሰማራቸው ገዳዮች ሬሳ በየሜዳው ወድቆ ማየትን የሚያክል ኣሳዛኝ ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ይህ ኣሰቃቂ የግፍ ግዲያ የማንንም እናትና ኣባት ኣንጀት ያቆስላል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ከኦሮሞ እናቶችና ኣባቶች በስተቀር ድምጻቸውን ያሰሙ ኣልታዩም። በተለይም በሃገሪቷ ይህን መንግስት እንቃወማለን የሚሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኣንዳችም ድምጽ ኣለማሰማታቸው ይገርማል፣ ያሳዝናልም። ሁላችንም ይህን መንግስት በማስወገድ ፍትሕ ሰላምና እኩልነት በሃገሪቷ እንዲሰፍን እንፈልጋለን። ነገር ግን መሰረታዊ የሰዎች ልጆች መብት ላይ እንኳን ለመስማማትና ለመተባበር ኣልቻልንም። ይህም ተደጋግሞ እንደተነገረው ለኣፋኙና ጸረ-ዲሞክራሲ ለሆነው ቡድን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ መንግስት ሊወገድ የማይችለው በጥንካሬው ሳይሆን በእኛ በተለይም ፖለቲከኞች ኣለመስማማት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ኣምባገነኑ መንግስት ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ መርዝ እየረጨባቸው ተንገዳግደው ሲወድቁ በጥይት በሚጨርሳቸው ጊዜ እንኳን ኣለመቃወም ማለት የተቃዋሚነት ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለመረዳት ያዳግታል። ይህ በኣዲስ ኣበባ ዙሪያ በሚኖሩ የኦሮሞ ገበሬዎችን ከተማ ለማስፋት ተብሎ የሚወሰደው የማፈናቀል እርምጃን መቃወም ሁሉንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በዚህ ኣካባቢ የሚኖሩት ሌሎች ኣማራ፣ ወላታ፣ ከምባታ፣ ሲዳማ ወይም ሌሎች ቢሆኑ ተመሳሳይ ግፍ ስለሆነ የሚፈጸምባቸው ለመብታቸው መቆማቸው ኣይቀርም ነበር። ስለዚህ ኦሮሞ ይህንን ህገወጥ ወረራ መቃወሙ ማንኛውም ሰባዊ ፍጡር የሚያደርገው የመብት ማስከበር ጥያቄ ነው እንጂ የሌሎችን ጥቅም የሚጎዳ ተደርጎ ሊታይ ኣይገባም።
የኦሮሞ ህዝብ በገዛ ሃገሩ ላይ በሰላም መኖር ካልቻለ በምንም መልኩ ሌሎች በሰላም ሊኖሩ ኣይችሉም። ስለዚህ ኣምባገነኖችንና ጸረ ሰላም የሆኑትን ገዢዎች ከኦሮሞ ህዝብ ጎን ቆመን ካልተቃወምነውና ካላስወግደነው ሰላምም ሆነ እድገት ለሁላችንም ኣይመጣም። ምናልባት ገዢው መንግስት ኣሁን ባለው የወታደር ብዛትና መሳሪያ ተመክቶ የህዝባችንን ተቃውሞ የሚያቆም ሊመስለው ይችላል። የህዝቦችን ሃይል በወታደር ብዛትና መሳሪያ ለማቆም እንደማይቻል ኣሁን ያለው ገዢው መንግስት በሚገባ ያውቃል። መተማመኛው ሃይል ሳታሰብ ኣንድቀን ይከደዋል። ያኔ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሲሆን የኢትዮዽያ ኣንድነትም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫው ላይ እንዳስጠነቀቀው ኣደጋ ላይ ይወድቃል። ምናልባትም ታሪክ ሆኖ ይቀር ይሆናል። ስለዚህ ስለ የኢትዮዽያ ኣንድነት ብቻ የሚጨነቁ ወገኖች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ጭቆናዎች እንዲቆምና ይህ ሰላማዊ ህዝብ በተፈጠረበት ምድር ላይ ሙሉ መብቱ ተጠብቆለት ከሌሎች የሃገሪቷ ህዝቦች ጋር በሰላም እንዲኖር መደገፍና ከጎኑ መቆም ተገቢ ብቻ ሳይሆን ኣስፈላጊም ነው።
በመሆኑም በሃገሪቷ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ይግፍ ኣገዛዝ ወደት ሊያመራ እንደሚችል ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜ ኣሁን ነው። የኦሮሞ ህዝብ ለተፈጥሮና ህጋዊ መብቶቹ መከበር መታገሉን ያቆማል ብለው የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋል። ገዢው መንግስትም በሃይል ኣስቆማለሁ በማለት ህጻናትን እየፈጀ ይገኛል። ግን ፈጽሞ ሊያቆመው ኣይችልም። የማን ህዝብ የመብት ትግል እንደቆመ የኦሮሞ ትግል ይቆማል? ስለዚህ ሁላችንም ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም ጭምር ስንል ይህን ኣምባገነን መንግስት በለጋ ህጻናት ላይ የሚያካሄደውን ጭፍጨፋ ማውገዝ ኣለብን የሚል እምነት ኣለኝ። የሁላችንም መብት መከበርና እንደ የኣለም ህዝቦች በነጻነት፣ በእኩልነትና በመከባበር መኖር የሚንችለው ተባብረን ይህን ኣምባገነን መንግስት ሲናስወግድና ዳግም ለኣምባገነኖች ላለመገዛት ሲንወስን ብቻ መሆኑን ተገንዝበን፣ የፖለቲካን ትርፍና ኪሳራ ማስላት ትተን ለዘመናት በሁዋላ ቀር ኣገዛዞች ምክንያት ለም ሃገር እያለ በረሃብ ኣለንጋ ሲገረፉ ለኖሩትና እየ የኖሩ ላሉት ህዝቦች ስንል ግፍን ለማስወገድ መተባበር የውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ከደብተራቸውና ኣሬንጓዴ ቅጠል ሌላ ነገር ባልያዙት ህጻናት ተማሪዎች ላይ መንግስት ባሰማራቸው ገዳዮች ጭፍጨፋ ሲካሄድ እያዬ ዝምታን የሚመርጥ አንጀት ሊኖር ኣይችልም፣ ኣይገባም።
* በቀለ ጅራታ (የኦፌዴን የቀድሞ ዋና ፀሐፊ) – ከስዊድን
No comments:
Post a Comment