ለ18 ዓመታት በስራ ላይ የቆየው ሕግ
ሕገመንግስትን ይጥሳል ተባለ
ታህሳስ ፳፬( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌዴሬሽን ምክርቤት ላለፉት 18 ዓመታት በስራ ላይ የነበረውና የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት ጉዳያቸው የታየበት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8 ተራ ቁጥር 1 እና የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7 ተራቁጥር 1 ሕገመንግስቱን እንደሚጥሱ በመወሰን የመላኩ ፈንታን አቤቱታ ውድቅ አደረገ፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ በሚኒስትር ማዕረግ ሆነው ሲሰሩ ስለቆዩ የተከሰሱበት ጉዳይ መታየት ያለበት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ነው ወይስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚለው ጭብጥ ላይ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በሃላ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር
25/88 አንቀጽ 8-1 እና የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7-1 የህገመንግስቱን አንቀጽ 20-6 ይጥሳሉ ወይስ አይጥሱም የሚለው ነጥብ ሕገመንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለምክርቤቱ በመራው መሠረት ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክርቤትን አባላትን በዛሬው ዕለት ለሁለት ከፍሎ አከራክሮአል፡፡