Thursday, 2 January 2014

በደቡብ ክልል የይርጋ ጨፌ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ

ታህሳስ ፳፫( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መምህራኑ አድማውን የጀመሩት ያለፍላጎታችን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ደሞዛችን እየተቆረጠብን ነው በሚል ነው። መምህራኑ ለይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር፣ ለጌዲዮ ዞንና ልክልሉ ትምህርት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ” ከ ሀምሌ 2005 ዓም ጀምሮ ለህዳሴ ግድብ የሚቆረጠው ገንዘባችን እኛ ያለፈቀድነውና ያልተስማማንበት በመሆኑ ጥቅምት 28፣ 2006 ጀምሮ  ስራችንን በአግባቡ እየሰራን የመብት ጥያቄያችንን ለሚመለከተው ሁሉ ስናቀርብ በመቆየታችን ታህሳስ አንድ በዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢነት የከተማው ከንቲባ ፣ የከተማው ትምህርት ዩኒት ሃላፊ በተገኙበት አቆራረጡ አግባብነት የሌለውና የመምህራንን መብት የጣሰ መሆኑን በውይይቱ ተረጋግጦ ከታህሳስ ጀምሮ የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆም፣ መወሰኑን” አስታውሷል። ድብዳቤው “ነገር ግን የከተማው አመራር እንደተለመደው በመዋሸት እንዲቆም የተወሰነው ገንዘባችን እንዲቆረጥብን አድርጓል” ይላል።

ድብዳቤው አያይዞም ” የታህሳስ ወር የተቆረጠበን ተስተካክሎ እንዲከፈለን፣ ከሀምሌ 30 ፣ 2005 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ወራት የተቆረጠብን ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለስልን፣ ከዚህ ቀደምም ያለፈቃዳችን እየተቆረጠብን ያለው የኢች አይ ቪ መዋጮ እንዲቆም እየጠየቅን ከዛሬ ማለትም ከታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓም ጀምሮ ስራ ማቆማችንን እንገልጻለን፤ የታህሳስ ወር የሚመለስልን ከሆነ ግን ወደ ስራ ገበታችን ተመልሰን እየሰራን ከዚህ ቀደም የተቆረጠውን  የ5 ወር ገንዘባችንን ደግሞ እስከ ታህሳስ 25 2006ዓም በትእግስት የምንጠብቅ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን አሁንም ስራችንን ለማቆም የምንገደድ እና ለሚመለከተው የበላይ አካል የምንሄድ መሆናችንን ከወዲሁ እናሳውቃለን” ብሎአል።  በትምህርት ቤቱም  ይሁን ከትምህርት ቤት ውጭ ለሚፈጠሩ ችግሮች  መምህራኑ ተጠያቂዎች ያለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ደብዳቤውን ተከትሎ መምህራኑ ያስራ ማቆም አድማውን ተማሪዎችን በማሰናበት መጀመራቸውን ተከትሎ መስተዳድሩ ዛሬ የታህሳስን ወር ለመክፈል መገደዱን ዘግይቶ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በደቡብ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ያለፈቃዳቸው የሚቆረጥባቸውን ገንዘብ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

No comments:

Post a Comment